1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶማሊላንዷ ሀርጌሳና በርበራ ወደብ በጋዜጠኛው ዕይታ

ዓርብ፣ ሚያዝያ 18 2016

ሶማሊላንድ ከሶማሊያ እራሷን በመነጠል እራስ ገዝ ከሆነች ሦስት አስርት ዓመታት አለፉ። ዛሬም ግን ሶማሊላንድ እንደ ሀገር ዓለም አቀፍ እውቅና አላገኘችም።

https://p.dw.com/p/4fEeA
የሶማሊላንድ ዋና ከተማ ሀርጌሳ
የሶማሊላንድ ዋና ከተማ ሀርጌሳምስል Eshete Bekele/DW

የሶማሊላንዷ ዋና ከተማ ሀርጌሳ ወቅታዊ ገጽታ

ሶማሊላንድ ከሶማሊያ እራሷን በመነጠል እራስ ገዝ ከሆነች ሦስት አስርት ዓመታት አለፉ። ዛሬም ግን ሶማሊላንድ እንደ ሀገር ዓለም አቀፍ እውቅና አላገኘችም። ዋና ከተማዋ ሀርጌሳ በርካታ ተሽከርካሪዎችን የምታስተናግድና ግዙፍ ከተማ መሆኗን በቦታው ተገኝቶ አካባቢውን የቃኘው ባልደረባችን እሸቴ በቀለ ይናገራል። የሶማሊላንድ ወደብ በርበራ ትልቅና በርካታ እንቅስቃሴዎችን የሚያስተናግድ እንደሆነም ተመልክቷል።ሶማሊላንድ የተሻለ ሕይወት በሌላ ሀገር ለማግኘት የተመኙ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከሚተላለፉባቸው የመሸጋገሪያ ሃገራት አንዷ እንደመሆኗም እጅግ ብዙዎችን በዚያ አግኝቷል። በተቃራኒው እዚያው ሶማሊላንድ ውስጥ ሀርጌሳም ሆነ በርበራ በተለያዩ ሥራዎችን እና የንግድ መስኮች ተሰማርተው ጥሩ የሚንቀሳቀሱ፤ በተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችም ውስጥ የሚሠሩ ኢትዮጵያውያንምም የማየት ዕድሉን አግኝቷል።

ፎቶ፤ ሀርጌሳ ከተማ
ሶማሊላንድ ከሶማሊያ እራሷን በመነጠል እራስ ገዝ ከሆነች ሦስት አስርት ዓመታት አለፉ። ፎቶ፤ ሀርጌሳ ከተማ ምስል Eshete Bekele/DW

ባለፈው ታኅሣሥ ወር ማለቂያ በጎርጎሪዮሳዊው የዘመን ቀመር ደግሞ በ2024 የመጀመሪያ ቀን የኢትዮጵያ መንግሥትና ራስገዟ ሶማሊላንድ የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውን ይፋ አድርገዋል። በመግባቢያ ሰነዱ መሠረት ኢትዮጵያ በሊዝ ለ50 ዓመት የሚዘልቅ ለንግድ እና ለባሕር ኃይል የሚሆን 20 ኪሎ ሜትር ወደብ ታገኛች። ለሶማሊላንድ መንግሥትም የሀገርነት እውቅናን ለማግኘት የመጀመሪያዋ ሀገር እንደምትሆን ታስቧል። ስምምነቱ በሶማሊያ መንግሥት በኩል ከፍተኛ ተዋውሞ ያስከተለ ሲሆን ግብጽና የተለያዩ የአረብ ሃገራት ጉዳዩን የሶማሊያን መንግሥት ሉዓላዊነት ያከበረ አይደለም በሚል ተቃውሞና ትችት አሰምተዋል። ለመቃዲሹ መንግሥትም ድጋፋቸውን ሰጥተዋል። እስካሁን የተዳፈነ የመሰለው የሶማሊላንድ እና የኢትዮጵያ መንግሥት ስምምነትን ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴው እንደቀጠለ ነው እሸቴ በቀለ ያነጋገራቸው የሀገሪቱ ባለሥልጣናት የገለጹት።  

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ