1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርትኢትዮጵያ

«የሚፈርም ኃላፊ የለም» 2 ወር ደሞዝ አልተከፈለም

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 29 2016

በአማራ ክልል የሰሜን ጎጃም ዞን ጎንጂ ቆለላ ወረዳ መምህራን ደመወዝ ከተከፈላቸው ከ2 ወራት በላይ መሆኑን ዐስታወቁ ። የሚሰጣቸው ምክንያት ደግሞ፦ «የሚፈርም ኃላፊ የለም» የሚል እንደሆነ መምህራን ተናግረዋል በወረዳው 1ሺህ282 መመህራን አሉ ። የዞኑ አስተዳደር ደግሞ ደመወዝ እንዲከፈል ከወረዳ አስተዳደሩ ጋር መወያየቱን አመልክቷል ፡፡

https://p.dw.com/p/4faN5
Birr - Äthiopien Währung
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

በ ጎንጂ ቆለላ ወረዳ 1ሺህ282 መመህራን አሉ

በአማራ ክልል የሰሜን ጎጃም ዞን መምህራን ደመወዝ ከተከፈላቸው ከ2 ወራት በላይ መሆኑን ዐስታወቁ ። የሚሰጣቸው ምክንያት ደግሞ፦ «የሚፈርም ኃላፊ የለም» የሚል እንደሆነ መምህራን ተናግረዋል ። የወረዳው መምህራን ማኅበር በበኩሉ ደመወዝ እንዲከፈል ለማድረግ ያደረግሁት ጥረት ሊሳካ አልቻለም ብሏል ። የዞኑ አስተዳደር ደግሞ ደመወዝ እንዲከፈል  ከወረዳ አስተዳደሩ ጋር መወያየቱን አመልክቷል ፡፡

በአማራ ክልል አዲስ በተቋቋመው የሰሜን ጎጃም ዞን አስተዳደር የሚገኘው የጎንጂ ቆለላ ወረዳ መምህራን ደመወዝ ከወሰዱ ከ2 ወራት በላይ በመሆኑ ለተለያዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መዳረጋቸውን ተናግረዋል፣ ደመወዝ ለመውሰድ መምህራኑ ያደረጉት ጥረትም በተለያዩ አስተዳደራዊ ችግሮች እንዳልተሳካ ነው የሚገልፁት፡፡

አስተያየታቸውን ከሰጡን መምህራን መካከል አንዱ፦ « እነሱ (ወረዳ አስተዳደር አመራሮች) እንደሚሉት የሚፈርም ሰው የለም፣ የተወከሉ ሰዎች ነበሩ እነርሱ መፈረም ነበረባቸው፣ እነርሱ ባለመፈረማቸው ምክንያት ክፍያ አልተፈፀመም፣ በጣም ዝቅተኛ የሆነ ክፍያ ነው መምህራን የሚከፈለን፣ አርሷም ብትሆን አልተከፈለችንም» ብለዋል፡፡

ሌላው አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው የወረዳውን አስተዳዳሪ አቶ ጌታቸው ጋሻውን ለማነጋገር ቢሞክሩም የወረዳው ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ ባለመኖሩ ደመወዝ መክፈል እንዳልተቻለ እንደተገለፀላቸው አመልክተዋል፡፡

አክለውም፣ " ደመወዝ ከተቋረጠብን 2 ወራችን ነው፣ አሁን 3ኛ ወሩን እየያዝን ነው፣ የወረዳውን ዋና አስተዳዳሪ እኔ ራሴ ሄጀ አነጋግሬዋለሁ፣ "የትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ የተወከለ ስለሌለ ነባር አመራሮችም አንገባም በማለታቸው፣ የወከልናቸውም መግባት ባለመቻላቸው ልንከፍል አንችልም” አሉን፣ ቢቸግረን አንድ ባለሞያ አስገብተን የክፍያ ሰነድ አዘጋጅተን ብንሰጣቸውም ደመወዝ ለመክፈል ፈቃደኛ አልሆኑም” ነው ያሉት፡፡

የጎንጂ ቆለላ ወረዳ መምህራን ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ዘሪሁን መኮንን ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት አስተያየት ችግሩ እንዲፈታ የተለያዩ ጥረቶች ቢያደረጉም ሊሳካላቸው እንዳልተቻለ ገልጠዋል ። ከመምህራን በተጨማሪም አንዳንድ የጽ/ቤት ኃላፊ ያልተመደበላቸው ወይም ቢመደብላቸውም መግባት ያልፈለጉ ኃላፊች ያሏቸው  የመንግስት ሠራተኞችም ደመወዝ እያገኙ አይደለም ብለዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ጉዳዩን ከወረዳ እስከ ዞን ባሉ አስተዳደራዊ መዋቅሮች ቢያደርሱም” ጆሮ የሚሰጠን የለም” ሲሉ ገልፀዋል፡፡

የአማራ ክልል መልክዓምድር ገጽታ ። ፎቶ፦ ከማኅደር
የአማራ ክልል መልክዓምድር ገጽታ፥ ላሊበላ አካባቢ ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Sergi Reboredo/picture alliance

የወረዳውን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጌታቸው ጋሻውን "የሚፈርም አካል ለምን አልተመደበም?” ብለን ለመጠየቅ በተደጋጋሚ በእጅ ስልካቸው ላይ ያደረግነው ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ፣ ስልካቸውን ማንሳት ባለመቻላቸው አልተሳካልንም፡፡

የሰሜን ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሰፋ ጥላሁን ስለጉዳዩ ይፋዊ ቅሬታ እንዳልደረሳቸው አመልክተው፣ ሆኖም ከከተለያዩ ምንጮች  በሰሙት መረጃ መሰረት የመምህራን ደመወዝ አልተከፈለም፡፡ የመምህራን ደመወዝ ባስቸኳይ እንዲከፈል ከወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ጋር መወያየታቸውንና መግባባታቸውን አመልክተዋል፡፡

በጎንጂ ቆለላ ወረዳ 4 የሁለተኛና 48  የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ 1ሺህ282 መመህራንና ከ20ሺህ በላይ ተማሪዎች እንደሚገኙ ከወረዳው መምህራን ማህበር ገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡

ዓለምነው መኮንን

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር