1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኧልሸባብና ረሐብ፦ የሶማሊያው ፕሬዚደንት ተግዳሮት

ቅዳሜ፣ መስከረም 7 2015

ብርቱ የረሐብ አደጋ እና የአሸባሪዎች ጥቃት ለሶማሊያው አዲሱ ፕሬዚደንት ጠንካራ ተግዳሮቶች ሆነዋል። ፕሬዚደንቱ ሰሞኑን ወደ ዩናይትድ ስቴትስ አቅንተው ስለዚሁ ተግዳሮት ጉዳይ ከአሜሪካ ባለሥልጣናት ጋር ተወያይተዋል። ረሐብ እና ሽብር ለአዲሱ የሶማሊያ ፕሬዚደንት ብርቱ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ቀጥለዋል።

https://p.dw.com/p/4Gzu9
Somalia mehrere Tote bei Angriff auf Hotel Hayat in Mogadischu
ምስል Feisal Omar/REUTERS

ጠኔ አስግቷል

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በዓለም ዙሪያ 345 ሚሊዮን ሰዎች የረሐብ አደጋ እንደተጋረጠባቸው ሐሙስ ዕለት ይፋ አድርጓል። ረሐብ እጅግ ካሰጋቸው ሃገራት መካከልም የመን፣ ደቡብ ሱዳን፤ ኢትዮጵያ፣ ናይጀሪያ እና ሶማሊያ ይገኙበታል ተብሏል። ጎረቤት ሶማሊያ ከአንዣበበባት የረሐብ ስጋት ባሻገር ኧል ሸባብ የተባለው ታጣቂ ቡድንም ሌላ ራስ ምታት ፈጥሮባታል። ረሐብ እና ሽብር ለአዲሱ የሶማሊያ ፕሬዚደንት ብርቱ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ቀጥለዋል። 

ከሦስት ወራት በፊት የተሾሙት የሶማሊያ ፕሬዚደንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ በሀገራቸው አደገኛ ረሐብ እና ኧል ሸባብን የመዋጋት ዘመቻ ይጠብቃቸዋል።  ፕሬዚደንቱ በተለይ ኧል ሸባብብን በመዋጋቱ ረገድ ከሰሞኑ አመርቂ ድሎችን እንዳስመዘገቡ ተነግሯል። ባለፈው ሳምንት እሁድ የሶማሊያ ጦር ሠራዊት ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመተባበር 20 መንደሮችን ከኧልሸባብ ነጻ ማውጣቱን የሀገሪቱ የመረጃ፤ ባህል እና ቱሪዝም ሚንሥትር በትዊተር ገጹ ይፋ አድርጓል። በዘመቻው በመቶዎች የሚቆጠሩ የኧልሸባብ ሚሊሺያዎች መገደላቸውም በትዊተር መረጃው ተገልጧል። 

Al-Schabaab Miliz in Somalia
ምስል Tobin Jones/Au Un Ist/dpa/picture alliance

ሶማሊያ በኧል ሸባብ ላይ የጀመረችውን ዘመቻ እንድታጠናክር ዩናይትድስ ስቴትስ ግፊቷን ቀጥላለች። የአሜሪካ መከላከያ ሚንሥትር ሊዮድ አውስቲን የሶማሊያው ፕሬዚደንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድን ፔንታገን ድረስ ጠርተው በዚሁ ጉዳይ አነጋግረዋል።  ሶማሊያ ኧል ሸባብ ላይ በምታካኺደው ዘመቻም የአሜሪካ ድጋፍ እንደሚቀጥል መከላከያ ሚንሥትሩ አረጋግጠዋል።  

«አል ሸባብ በሐምሌ ወር ወደ ኢትዮጵያ ግዛት በኃይል ከገባ በኋላ ነሐሴ ወር ውስጥ የሶማሊ መር ዘመቻ መደረጉን በመስማቴ ተበረታትቼ ነበር። እዚህ ያለው ዘመቻችን እጅግ ወሳኝ ነው የተከበሩ ፕሬዚደንት። እናም ከዚህ ነውጠኛ ኃይል ራሳችሁን እንድትከላከሉ ለመርዳት እንደ አጋር ምንጊዜም ዝግጁ ነን።»

ኧል ሸባብ ባለፈው ሐምሌ ወር በኃይል ኢትዮጵያን ለመውረር መጠነ ሰፊ የጥቃት ሙከራ አድርጎ ነበር። በኢትዮጵያ ጦር በተሰነዘረበት ምት ግን ከፍተኛ የሰው እና የንብረት ኪሳራ ደርሶበት በመጣበት መመለሱ ቀደም ሲል ተዘግቧል። የተረፈው የኧል ሸባብ ርዝራዥ ወደ ሶማሊያ ከሸሸ በኋላ ደግሞ የሶማሊያ መንግሥት ከአየር በተደገፈ ድብደባ ብርቱ ጥቃት እንዳደረሰበት ተገልጧል። የሶማሊያ መንግስት ከአየር የሚደረገውን ድጋፍ ያገኘው ከዩናይትድ ስቴትስ ይሁን ከሌላ ዐይታወቅም። ፕሬዚደንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ሐሙስ ዕለት ከፔንታገን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ሲነጋገሩም  ዩናይትድ ስቴትስ ስለምታደርግላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። 

«ክቡር መከላከያ ሚንሥትር በድጋሚ አመሰግናለሁ። ለእኔ እዚህ መሆን ከፍተኛ ደስታ እና ታላቅ ክብር ነው የፈጠረልኝ። የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት አል ሸባብን በመዋጋት ዙሪያ እና አሳሳቢ እየኾነ በመጣው የሰብአዊ ጉዳዮች ሒደት ከሶማሊያ ሕዝብ ጋር ላለው ስልታዊ ትብብር ምስጋናዬን ማቅረብ እሻለሁ።»

Somalia Präsident Hassan Sheikh Mohamud
ምስል Farah Abdi Warsameh/AP/picture alliance

ፕሬዚደንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ኧል ሸባብን ከውጊያ ባሻገርም መቅረብ እና መወያየት ያስፈልጋል የሚል አቋም ያላቸው ናቸው። ያን አቋማቸውን ባስተጋቡበት ወቅትም ነበር ሞቃዲሾ ውስጥ ለ15 ዓመታት ጥቃት ሲሰነዝር የነበረ የቀድሞ የኧል ሸባብ ቃል አቀባይ ሙክታር ሮቦውን አዲሱ የእምነት ጉዳዮች ሚንስትር አድርገው የሾሙት። 
ፕሬዚደንቱ ሀገራቸው ኧል ሸባብን በመዋጋቱ ረገድ ስለሚገጥማት ተግዳሮት ሲገልጡ ሶማሊያ ከኢትዮጵያ እና ኬንያ ጋር የምትዋሰንባቸውን ረዣዥም ድንበሮችን ጉዳይም አንስተዋል። 

«ከኢትዮጵያ እና ኬንያ ጋር ረዥም ድንበር አለን። በሁለቱም ድንበሮች በኩል የሚኖሩት ሶማሌዎች ናቸው። ስለዚህም ኧል ሸባብ በዚህ እጅግ ሰፊ በሆነው ድንበር በኩል ለመጓዝ እጅግ በጣም ቀላል ነው።»

ፔንታገን የአሜሪካ መከላከያ ሚንሥትር ሊዮድ አውስቲን እና የሶማሊያው ፕሬዚደንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ካደረጉት ውይይት በኋላ ባወጣው መግለጫ፦ «ሁለቱ በአፍሪቃ ቀንድ ስላለው የፀጥታ ኹኔታ» ተነጋግረዋል ብሏል። በውይይቱ «በቀጠናው ስለሚታየው አስደንጋጩ የአየር ንብረት ለውጥ፤ የሰብአዊ ቀውስ፤ ግጭት እና የአደገኛ ጽንፈኞች ስጋት» መነጋገራቸውም በመግለጫው ተጠቅሷል። 

Somalien Minister für religiöse Angelegenheiten Muktar Robow Abu-Mansur
ምስል Ali Elmi/AFP

ሶማሊያ በእርግጥም ከፍተኛ የሰብአዊ ቀውስ ስጋት ከተጋረጠባቸው ሃገራት መካከል አንደኛዋ ናት። በሀገሪቱ የዘለቀው ግጭት እና ውጊያ ከከባቢ አየር ለውጥ ጋር ተደማምሮ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሶማሊያውያን ብርቱ የረሐብ አደጋ እንዲደቀንባቸው አድርጓል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች እና የአስቸኳይ ርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ ዋና ኃላፊ ማርቲን ግሪፊትስ ሶማሊያ እና ጎረቤቶቿ ላይ ያንዛበበው ጠኔ እጅግ አስግቷቸዋል። 

«ረሐብ ሶማሊያ ውስጥ ይከሰታል። ታዲያ ብቸኛው ቦታው ያ ብቻ አለመሆኑም ያስፈራናል።» 

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ርዳታ በሚሰጥባቸው በዓለም ዙሪያ 345 ሚሊዮን ሕዝብ ወደ ረሐብ እየተመመ ነው ብሏል። የዓለም ምግብ ድርጅት (WFP) እና የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ (OCHA) የበላይ ኃላፊዎች ሐሙስ እለት ለፀጥታዉ ምክር ቤት ይህንኑ ስጋታቸውን ገልጠዋል።  ሶማሊያ የረሐብ ስጋት ካንዛበበባቸው ሃገራት ዋነኛዋ ናት።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ